እሳት ዐመድ ወለደ - ከሎሬት ፀጋዬ ገበረመድህን ቀዌሳ

ፀጋዬ-ገበረመድህን
ፀጋዬ-ገ-መድህን
ፀጋዬ

#1

“እሳት ዐመድ ወለደ”

"አባቴስ ወንድ ወለድኩ ይበል!
ወለድኩ ይበል ይልቅ፥ በቃ፥
በምላሱ እሚያመረቃ
ወኔው በአረቄ እሚነቃ
ልቡን በቧልት እሚደቃ
በሤራ በነገር አሽሙር
በታክት በእንትሪግ አዙር
ላሮጥ ላሽከረክር ላዞር
በብልጠት ባንደበት ንቃት፥ በመስሎ አስመስሎ መኖር
ሴቷን በነገር መብለጥለጥ፥ ጋለሞታን በምላስ ጦር
ሁሏን ረትቼ አሸንፌ፥ በምጸት ወግ፥ በጌጥ፥ በአሞር
ሲነጋ እንደአመድ አፋሽ ገል
ሲመሽ እንደሽንቁር በርሜል
የአግቦ ጢስ በማንቃረሩ
ወሬ በማንሸራሸሩ
ተሞልቶ በምተርተሩ፥
ነፋስ ጠብቶ አየር ታልቦ
የነገር ረሃብ ተርቦ
ጉድ በማናፈስ ተስቦ
ከዚህ ቅድቶ እዚያ ዘንቦ
ውሃ እንደማይቋጥር ገንቦ…

ላባቴ ተወልጀለት፥ ቅምጥል የልቡ ኩራት
ግሥላ የወኔው እሳት
ይመካ እንጂ ይንቀባረር
ይሞካሽ እንጂ የገደር
የዘር ወጉ እንዳይደፈር
ደርሼለት እሱን መሰል
በተከለው እሚከተል
አባቴስ ወንድ ወለድኩ የበል።

መሰል ወራሽ ተካሁ ይበል የዘር ቅርሱን የሚያስፋፋ
ድል የሚመታ ስተቴ፥ በነገር በአሽሙር ልፈፋ
በአግቦ እንደቅኔ ዘረፋ
በሽሙጥ ባፍ ዘለፋ፥
ይበል እንጂ እኔም ወንድ ወለድኩ
ባፍ እሚበልጠኝ አደረስኩ
በነገር እሚጥል ፈጠርኩ፥
ያባት ልጅ ያዘው ቅምጥል
የደም ትክል የወኔው ሽል፥
ፈጠርኩ ይበል ዘበዝባዛ፥ እንደአዙሪት እሚፈትል
በምላስ ቀስጥ አነጣጥሮ፥ ቂም በልቦና እሚተክል
ደም በደም እሚያስተጣጥብ፥ ወገን ከወገን እሚያክል
እንደስራስር ደብተራ፥ ላንቃው መርዝ እሚያቀላቅል
ውጋቱ ዘር እሚያጣጥል
እንደጦስ እሚደበልል
እንደዛር ውላጅ አሽሮ
ያጥንት ሰባሪ አቅሮ
አንደበቱ እንደወስፈንጥር፥ ሾሎ ናስተናግር ቅጠል
አፈጊንጥ ያብሾ ጡት ልጅ፥ ጥላ ወጊ ቀትረ ፈልፋል
አለሳልሶ እንደወላፈን፥ አሸልቦ ሲንበለበል
በከንፈር ፈግታ ከንፎ፥ ባፉ ጥላ ወግቶ እሚጋል፥
በከንፈር ፈግታ ከንፎ፥ ባፉ ጥላ ወግቶ እሚገል፥
ደምመራዥ ልጅ፥ ያፋፍ ላይ ድጥ፥ መስክ መሳይ ያሽሙር ደለል
የወሬ ማንፈሻ ጋሻ፥ ደርሼለት እሱን መሰል
በተከለው እሚከተል…
አባቴስ ወንድ ወለድኩ ይበል!"

‘ለተማሩ’ - ለማይማሩ አፈ-ሊቃውንት (፩፱፰፩ አዲሳባ)