አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ - ከሎሬት ፀጋዬ ገበረመድህን ቀዌሳ

tsegaye-gebremedhin
አቴቴዱብራ
ፀጋዬ-ገ-መድህን

#1

አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ

image

ለካ እንደትዝታ አስታምሞ
አንደዘነጉት የእናት ጡት፥ ከዘመን ጋር አገግሞ
ምንም ቢርቅ ምንም ቢሸሽ፥ ሕልሜ ከሕልምሽ ተዛሞ
በዓይንሽና በዓይኔ መሃል፥ የሃሰት ሥልጣኔ ቆሞ
ባንተያይ ባንወያይ፥ አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ
እንደልጅነት ሰመመን፥ ለካስ ዕድሜም ያማል ከርሞ።
ተግ ሲል ያንቺ ሽዉታ
ብዥ ሲል እንደአድባር ጥሪ፥ እንደተርብ ቅርስ ሽታ
እንደ እሳት ዳር ተረተ ግርሻ፥ እንደእንቆቅልሽ ትውስታ
የጥቅምት እሸት አወደ፥ ነቃ ደሞ ያንቺ ትዝታ…
አውድማው ትንደረከከ
ሰንበሌጥ ተንተረከከ
ነይ አክርማ እንነቃቅል፥
ከወንዛችን ሾላ ጠስል
ነይ ጢሎሽ እንንጠላጠል፥
መስኮቻችን ሰብሎቻችን፥ ግጦሾቻችን አባቱ
የአቴቴሽ ላሞች አጋቱ
በሮቻችንም አጓሩ፥ ኮርማዎቻችንም ነቁ
ጊደሮቻችን ለጥቃት፥ ለይዘታ ልክብደት በቁ
የሁዳድ ድርቆሽ ሠፈር፥ ጥገቶቻችን ቦረቁ፥
አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ፥ እጄን በትዝታሽ ያዢኝ
በሕልም ጣቶችሽ ሳቢኝ
መቸም … በውን አልሆንሽም፥ አንዲያው በሰመመን ዳሺኝ።
የኔ እጅ እኮ እርፍ አይጨብጥም
የኔ ክንድ ተልም አይተልምም
የኔ ጣት አረም አይነቅልም
በፊደል መፈደል በቀር፥ ጉልጓሎ እኮ አይጎለጉልም
ለስልሻለሁ፥ ሠልጥኛለሁ፥ ሰይጥኛለሁ አልሆንሽም፥
አቴቴ ዱብራ ቦረና
መቸም ሁሉን ቻይ ነሽና
አጥንቴን ከአጥንትሽ ማዕድን፥ ቢመነጭም ተቀምሞ
ከ"ሀ"ና ከ"አሐዱ" በፊት፥ ከቃል በፊት አስቀድሞ
ዛሬ በዓይንሽ በዓይኔ መሀል፥ አጉል ሥልጣኔ ቆሞ
ስየጠንኩና አልሆንሽ አልኩ፥ አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ፥ …
አዎን መቻል ባንቺ ያምራል፥ ያን የትዝታ ሰቀቀን
ያን የልጅነት ሰመመን
ከዓመት ዓመት ተሽጋግረን፥ አዳዲስ ዘመን ሲሰለፍ
ሰንበሌጡ ሲንተረከክ፥ የአዝመራ እሸት ሲትረፈረፍ
የማር እሸት እንቁረጥ ተይ፥ የጥቅምት አበባ እንቅጠፍ
ነይ ሸጎዬ አብረን እንግዘፍ
ጣት ለጣት እንቆላለፍ
በዓይን ጥቅሻ እንገራረፍ
ከአውድማችን አፋፍ ለአፋፍ፥ በዳሰሳ እንጠላለፍ
ተይ ፍቅር እንዘራረፍ
በሕልም እንኳ እንተቃቀፍ፥ …
አቴቴ ዱብራ ቦረና፥ አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ
የቀን የጊዜ እንቆቅልሽ፥ በሕልም መርፌ ተጠቅሞ
በየመከሩ ተተልሞ
እንደዘነጉት የእናት ጡት፥ ከዘመን ጋር አገግሞ
ምንም ቢርቅ ምንም ቢሸሽ፥ ሕልሜ ከሕልምሽ ተዛሞ
በዓይንሽና በዓይኔ መሃል፥ አጉል ሥልጣኔ ቆሞ
ባንተያይ ባንወያይ፥ እንደጥንቱ እንደቀድሞ
እንደልጅነት ሰመመን፥ ዕድሜም እኮ ያማል ደሞ…
አዎን ዕድሜም ያማል ከርሞ…

  • ሌአቴቴ ዱብራ ኦሮሞ (ባሌ ጎባ), ከሎሬት ፀጋዬ ገበረመድህን ቀዌሳ