ኢልማ ገልማ - ከ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ቀዌሳ

ኢልማ-ገልማ
ፀጋዬ-ገ-መድህን

#1

ኢልማ ገልማ
አባ ገዳ ርቱእ ጀማ
ብፁእ ጀማ
ለካ አንተ ነህ
አባ ገዳ ኢልማ ገልማ
ያደ ኦሮሞ ሻማ
ዋቃ ገዲ ነማ ኦሊን ሱማ
አከ ሱማ
የተሰኘዉ እንደ አክሱም
የተባልከዉ ፍፁም ጀማ
ለካ አንተ ነህ
አገ ኦጋ
ጂገ ሎጋ
አባ ሰርዳ
አባ ገዳ
አባ ፈርደ ነበልባሉ
እም ቅድመ ኦሪት ባህሉ
ያኢ ቢያ አባ ቃሉ
የማይቀለበስ ቃሉ
ለካ አንተ ነህ
ሴራ አርካ ኦገ ገዳ
የአድባር ዋርካ
ያዴ እናቴ
ያዴ እስቴ
ያዴ አተቴ
ያዴ እቴቴ
ያቴ ሆራ የኩሽ ነዶ
አባ ቦኩ አከም ኢዶ
በአናትህ ፀሃይ ከለቻ
የምትጠልቅ አንተ ብቻ
የካም ኢደ ኢዶ ምድር
ተነባቢ የአስር ሚስጥር
አባ ወሮ አባ ወራ
አባ ባሮ አባ በራ
የጅቡቲም ጀበ ዲሾ
የመቅዲሾም መቀ ዲሾ
የነሙንቴሳ ካም በልአ
እንደ ብራቡ ከምፐላ
መነ ደላ አከ መንደላ
መቀ ደላ አከ መቅደላ
የፊላኒ ካኖደላ
የምትሰኝ የምታሰኝ
የጎና ቤት አባ ወራ
የላሊ ቤት ላሊበላ
በጎፈሬህ ስሪት ላባ
አዶ አዶየ ዉብ ቀዘባ
አዳ የከለቻ ተሸላሚ
ያዱ ግንባር ተቀዳሚ
የአዲስ ዘመን መፀዉ አደይ
አዳ…አዱኛን እልል እሰይ
የምታሰኝ…የምትሰኝ
አዱ አዱኛ
አባ ቢሌ
የአካ ኪሌ
የአባ ቢሌ
ለካ አንተ ነህ
ገዳ ገዳም
የአለም ሰላም
ገዳ ቢሊሱማ ሳቃ
ፈካ ጉራቻ አካ ዋቃ
የመፀሃፍት አምላኩ አኒ
ያለበሰህ ድርብ ካኒ
የጥቁር ፈርኦን ልሳን
የአዴ አዳ ፀሃይ ብርሃን
የአዱሊስ አዱኛ ኪዳን
አባ ገዳ አባ በአል
የቅድመ አክሱማዊት ቃል
የአስርቱ በሮች መሰላል
የማለዳ ንጋት ፀዳል
የኦሩስ ኦሪሳ ተምሳል
ለካ አንተ ነህ
አገ ኦጋ
ጂገ ሎጋ
ያኢ ቢያ አባ ቃሉ
የማይቀለበስ ቃሉ
ርቱእ ጀማ
የተባልከዉ አባ ሱማ
እንደ አክሱማ
ያደ ኦሮሞ ሻማ
አባ ገዳ ኢልመ ገልማ
ለካ አንተ ነህ

-ቦረና : - ድሬ ሊበን
-ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ቀዌሳ