እስከመቼ ይሆን አዋሽ | ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ቀዌሳ, 1964

thsegaye-gmedhin
awash
laga-hawas
awash-river
poetry

#1

እስከመቼ ይሆን አዋሽ | ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ቀዌሳ, 1964


Photo Credits: Dagne Si’a!

እስከመቼ ይሆን አዋሽ

አዋሽ የመጫ ስር ፍሳሽ
የለም አፈርሽ ደም ቅናሽ
የሸዋ የእምብርትሽ ላቦት
የምንጮችሽ የምጥ አማጭ
የአለትሽ የተራሮችሽ የጉልጥምጥሚትሽ ፍላጭ
አዋሽ ህመምህ ምንድነው
ህመምክስ አንተስ ምንድነህ

ከዉሃ ወዝ የተለየ መቸስ ልዩ ንገርት የለህ
አንደ ሴቴ ሸረሪት ፅንስ እራስክን በራስህ ዋጥ ያለህ

እስከመቼ ይሆን አዋሽ
ሲያሳድድህ ሲያቅበዘብዝህ
ላትዘልቅ ላያዛልቅህ
አሸዋ ላሸዋ ድኸህ
ዉስጥ ለዉስጥ ምሰህ ጠልቀህ
የምድርን ማህፀን ቦርቡረህ
ዋልታዋን ቁልቁል ፈንጥረህ
እናትህ ዉቅያኖስ ማህፀን ላትገባ ትባክናለህ

እስከመቼ ይሆን አዋሽ
አዋሽ ቡርቃው
መጫ ምንጩ
ዳዳ ፅንሱ
ሸዋ ፍንጩ
ዉጠህ ተዉጠህ እርጩ
የንዳድ የበረሃ እጩ
ንገርትህ ምንድነው አዋሽ
አባ ብቻ አባ እቅጩ
ዘላለምክን ፈሰህ ባታልቅ
ምነው ተስፋ መቁረጥ አታውቅ
እስከመቼ ይሆን አዋሽ

አዋሽ በቃኝ ኣትል ቆራጥ
ማን ያስተማረህ ፈሊጥ ነው አርህ ለማለምለም መዋጥ
አሻቅበህ ወደምስራቅ ወደ ጀምበር መውጫ መናጥ
ሰምጠህ ልትቀር በሃሩር መኣት
አዋሽ ቡቡ ሮሮ ብርቁ የዘላለም ንዳድ ስንቁ
አዋሽ አባ ብቻ ጎዞ ዘላለም ብሶት ኣርግዞ
አነዋባየ ሸበሌማ ሰብረው ውቅያኖስ ሲዘልቁ
አንግዮን ወርደው አልፈው ሱዳንን ምስርን ሲያጠምቁ
ምነው ያንተ ጉዞ ብቻ በረሃ ላይ መታነቁ
እስከመቼ ይሆን ኣዋሽ
ወዝክን አሸዋ ሲውጥህ ደምክን በረሃ ሲመጥህ
ዘላለም አጥንትህን ሲመዘምዝህ
መች ይሆን በቃኝ የምትል መች ይሆን በቃህ የሚልህ

እስከመቼ ይሆን አዋሽ
አዋሽ የመጫ ስር ፍሳሽ
የዳዳ የቱላማ ደም በረሃ የምትደመደም
የሰባት ቤት ጉራጌ ኣድባር
የከረዩ ቅቤና ማር ፈሰህ ላሸዋ የምትዳር
እስቲ አንዴ እንኳን እንደነዋቤ ውቅያኖስ ግባ
ዘላለምክን በአሸዋ ሆድ ተዉጠህ ከምታነባ

ቆራጡ እንኵዋ አንተ ነበርክ የጀግኖች መፍለቅያ ኩሬ
የሰንጋ ፈረሰኞቹ የነሆርዶፋ ጨንገሬ
የስንቱ መጠጊያ ዋሻ አዋሽ ደኔ አዋሽ ዱሬ
የጥንተፍጡራን መደብ የቅድመ መልካ ካንቱሬ
አዋሽ በቃኝን አታውቅም
በምድር ማህፀን ካድማስ አድማስ ዘላልምክን ስታዘግም
ወርደህ ሟጠህ ተንጠፍጥፈህ አሜን ታከተኝ አትልም

መጫ ቁዋጥሮ ሸዋ ፀንሶ ሰባት ቤት ጉራጌ አርግዞ
ከዳዳ ምንጭ አርሲ እምብርት ከነቅሪቱ ተጉዞ
ካላባ ጣፋ ሼክ ሁሴን አዳል ሞቲ ሽሉን ይዞ
ከከረዩ መተሃራ ከኢቱ እስከ አፋር አምጦ
አሸዋ ነክሶ ቀረ አዋሽ ሳይገላገል ሸምጥጦ
እንደ ወላድ ሳይታረዝ ከነፀንሱ አርህ ሰምጦ
በምድረበዳ ጉሮሮ በረሃ ላንቃ ተውጦ ቀረ

እስከመቼ ይሆን አዋሽ
አዋሽ ሮሮ አባ ቅርሱ
የዘላለም ንዳድ ጉርሱ

አዋሽ ቡቡ በረኸኛ
የአርህ ሸለቆ በረኛ
የአሸዋ ዋሻ መተኛ
የበረሃ ዋናተኛ
የምድረበዳ ብቸኛ
የዘለአለም መንገደኛ

የአበቅቴ መወራረሻ
የእፅዋት እድሜ መቁጠርያ
በፀደይ አልባሳት ማእፀንት የዘመን ላቦት ወዝ ማጥሪያ
የእንቁጣጣሽ ማዳበርያ የአዝርእት ሰብል ማጥለያ
በክረምት የዶፍ ረከቦት የሰማይ ምጥ መቀበያ
የደመና እንባ ማጠቢያ የማዕበል ሰደድ ማከያ
የተራሮችን ለቅሶ ቻይ ይጅረት ምንጮች አዋይ
ጭምት መሳይ ያላመሉ ዘራፍ ባይ በመስክ ሙሉ
አባ ጭራቅ ኣክናፍ ቀንዶ አዋሽ ዘጠኝ እራስ ዘንዶ
ቁልቁል እንደ ምሽት ጥላ ከሰማየ ሰማይ ወርዶ
ሞልቶ ተንደላቆ ኮርቶ የሰንተአለም ምድር ጎርዶ
ቀይ ደመና ተከናንቦ ጋራ እንደ አሻንጉሊት አዝሎ
ስንቱን በረት እንደጉድፍ አዉተፍትፎ አንጠልጥሎ
አዉድማውን አንገዋሎ ዋርካዉን ግቻ አሳክሎ
አመንምኖ አሰልሎ እንደዘጠኝ በገና አዉታር በየረድፎ ተሰድሮ
ባገር ምድር ዙርያ ጥምጥም እንደመቀነት ተቋጥሮ

አዋሽ ቁጣ አባ ዱታ የሰማይ ጥጉ ቱማታ
አዋሽ አባ ሻኛው ጋራ ኩሩው እንደነ መተሃራ
የግርማ ሞገስ መርገፉ እስከነ ምድር አቀፍ ዘርፉ
አባ ገስግስ ሞልቶ ደራሽ አባ አደፍርስ አባ ኩርፋድ
ከተፍ እንደመብረቅ ግማድ
በምድር ቁና ድንገት ሲጣድ
አዋሽ ንፉግ አባ መአት
የገጠሬ አታምጣ መኣት
የገጠሬ አታምጣ ምጣት

አዋሽ ደርሶ ቀማው መብረቅ
አባ መዝረፍ መውሰድ መንጠቅ
ግሳንግሱን አግበስበሶ በምድረበዳ ለማጨቅ
ሀሩር ጉሮሮ ለማመቅ
አሸዋ ሆድ ለመጠቅጠቅ
ሀራም ብሎ አብሮ ለመጥለቅ
ምድረ ከርስ መቀመቅ

እስከመቼ ይሆን አዋሽ
አዋሽ ብኩን ምስጢረኛ
የጠፍር ፋኖ አባ ብቸኛ
የበረሃ መንገደኛ
የጨረቃ ግዞተኛ
አገር ሞት ወዲያ ላትሞት
ከሀገረ ምጥ ወዲያ ላታምጥ
እስከመቼ ይሆን ኣዋሽ
እራስክን በራህ የምትውጥ

አዋሽ አባ ሮሮ ሀገሩ
የአሸዋ ማህፀን ድንበሩ
የምድረአለም ኬላ በሩ
ኩሩ
ብሶት እንደልቡ
ቅምጥል የሸዋ ቡቡ
የሰማይ አድማስ ግድቡ
ንዳድ ስንቁ
አርህ ግቡ

እስከመቼ ይሆን አዋሽ
አዋሽ ቡቡ አባ ብሶት
የሰው ችግር ሳይደርስበህ
ስይቸግርህ የውነት እጦት
ላትዘልቀው ላያዛልቅህ ለማንም የትም የምትሞት
ታድያ እስከመቼ አዋሽ

አዋሽ የመጫ ወዝ ፍሳሽ
የሸዋ ይእምብርትሽ ላቦት የምንጮችሽ የምጥ አማጭ
የአለትሽ የተራሮችሽ የጉልጥምጥሚትሽ ፍላጭ
እስከመቼ ይሆን አዋሽ
ወዝክን አሸዋ የሚውጥህ
ደምክን በረሃ የሚማጥህ
አጥንትክን ምድረበዳ ሃሩር የሚመዘምዝህ

መጫ ቁዋጥሮ
ሸዋ ፀንሶ
ሰባት ቤት ጉራጌ አርግዞ
ከዳዳ ምንጭ አርሲ እምብርት ከነቅሪቱ ተጉዞ
አላባ ጣፋ ሼክ ሁሴን አዳል ሞቲ ሽሉን ይዞ
ከከረዩ መተሃራ ከኢቱ እስከ አፋር አምጦ
እንደወላድ ሳይታረዝ ከነፅንሱ አርህ ሰምጦ
በምድረበዳ ጉሮሮ በረሃ ላንቃ ተዉጦ
አሸዋ ነክሶ ቀረ አዋሽ ሳይገላገል ሸምጥጦ

እስከመቼ ይሆን አዋሽ
ተስፋ መቁረጥ የማታውቅ
ፈሰህ ተሟጠህ የማታልቅ
ጉዞህ በረሃ ሲታነቅ
ሀሩር ጉሮሮ ሲታጨቅ
አጥንትህ ጉልጥምጥሚትህ ምድረበዳ ሲታመቅ
እስከመቼ ይሆን አዋሽ ቆርጠህ ቀይባህር የማትዘልቅ
እስከመቼ ይሆን አዋሽ
መቼም ሌላ ንግርት የለህ
እንደ ሴቴ ሸረሪት ፅንሽ እራስክን በራስህ ዋጥ ያለህ

-ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ቀዌሳ, 1964