ጠባብነት እና ትምክህተኝነት - የአንድ ህወሀት ሁለት ገፅታዎች | Taye Danda’a | Taye Dande’a

ጠባብነት
ትምክህተኝነት
ህወሀት

#1

በዝህ ዓመት መሰከረም መጨረሻ ላይ የህወሀት ማዕከላዊ ኮሚቴ ተሰብስቦ ጠባብነትን እና ተምክህተኝነትን ለመታገል አንደወሰነ ሰምተን ነበር። በወቅቱ ስለጉዳዪ ምንም አስተያየት ባልሰጥም መገረሜ ግን አልቀረም። ያልተገረመ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም። ሁሌ ተመሳሳይ ቀልድ መስማት መልሶ መላልሶ ይገርማል።

ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በተለየ ሁኔታ ህወሀት ለመለወጥ ዝግጁ አይመስልም። ዛሬም አጭበርብሮ መኖር ይፈልጋል። ኦህዴድን “ጠባብ”፥ ብአዴንን ደግሞ “ትምክህተኛ” ብሎ በመገምገም አሸማቆ ሊያሽከረክራቸዉ ይመኛል። ግን ወቅቱ ይህን አይፈቅድም። ሁለቱ ድርጅቶች ራሳቸዉን በአንድነት የህዝባቸዉን የሰቆቃ ዘመን ለማብቃት ወስኗል። ህወሀት የወክቱን ሁኔታ በትክክል ቢረዳ ተጠቃሚ ይሆናል። የተለመደ አሰልቺ ሙዝቃ መደጋገም ራሱን ይጎዳል። ወደፊት ለመሄድ የራስን ችግር መዝኖ ትክክለኛ እርምጃ መዉሰድ ያስፈልጋል። ራስን መልአክ አድርጎ ሌላዉን ዲያብሎስ ማድርግ ከንቱ ልፋት ነዉ።

ቃላት ትርጉም አላቸዉ። ትርጉማቸዉ ከታወቀ ማንን እንደሚገልፁ ማየት አይቸግርም። ለመሆኑ ጠባብነት እና ትመክህተኝነት ምንድ ናቸዉ? ማንንስ ይመለከታሉ? እሰኪ በእዉነት ስለእዉነት አንነጋገር። በዝህ ወቅት ዋስትናችን እዉነት ብቻ ነዉ!

ማን ጠባብ እንደሆነ እና ማን ትምክህተኛ እንደሆነ ለመለየት የቃሎቹን ትርጉም እንይ። ጠባብነት ማለት “ብቻዬን ልጠቀም” በሚል ስሜት ሌሎች ወገኖችን ማግለል ሲሆን ትምክህተኝነት ደግሞ “ከሁሉም በላይ ነኝ” ብሎ ራስን ማኮፈስ ነዉ። ሁለቱ አመለካከቶች ፀረ-ሠላም፥ ፀረ-ልማት እና ፀረ- ዴሞክራሲ ናቸዉ። በአሁኑ ወቅትም እነዝህ አመለካከቶች ለኢትዮጵያ ጠንቅ መሆናቸዉ አይካድም። ህወሀት “የኢትዮጵያ ችግር ትምክህተኝነት እና ጠባብነት ነዉ” ማለቱ ትክክል ነዉ። ችግሩ “ጣባብ እና ተምክህተኛ ማነዉ?” የሚለዉ ነዉ። ጠባብነት በተሳሳቴ ሁኔታ የኦሮሞ መገለጫ ሆኖ ለ26 ዓመታት ሲያገለግል ኖሯል። ህወሀት “ጠባብነትን እታገላለሁ” ሲል ኦሮሞን ለመታገል ማሰቡ ይገመታል። ይህ ጠባብነትን አጣሞ ከመተርጎም ይነሳል። ትክክለኛ ጠባብ ህወሀት ነዉ። ሌሎችን በማግለል የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የተቆጣጠረዉ ህወሀት ነዉ። የውጭ ንግድ፣ የሀገር ዉስጥ ንግድ፣ የግንባታ ስራ፣ ኮንትሮባንድ እና ሌሎችም የሥራ ዘርፎች ከትንሽ እስከ ትልቅ በሱ እጅ ናቸዉ። ከሥልጣን አንፃርም አብዘኛዉን ለብቻዉ ይዟል። መዘርዘር አስፈላጊ አይደለም። መቼም ከዝህ በላይ ጠባብነት የለም። ስለዝህ ጠባብነት በተግባር የሚገኘዉ በህወሀት ቤት ነዉ። ትምክተኝነት ደግሞ የአማራ መገለጫ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። ከህወሀት አንፃር ትምክህተኝነትን መታገል አማራን መታገል ማለት እንደሆነ ይታመናል። ያም ትክክል አይደለም።

ትምክተኝነት በትክክለኛ ትርጉሙ ከታየ የህወሀት ባህሪ ነዉ። “እኔ ካልገዛሁ ኢትዮጵያ ትበታተናለች” እያለ የሚያስፈራራዉ ህወሀት ነዉ። ከሱ ሌላ ለኢትዮጵያ የሚያስብ የለም ማለቱ ነዉ። ጀግና እሱ ብቻ፥ ምሁር እሱ ብቻ… በሁሉ ነገር ላይ የበላይ መሆኑን ደጋግሞ ይተርካል። በሱ እይታ ህዝብ ስለራሱ አያዉቅም። ለሁሉም “እኔ አዉቅልሀለሁ!” ይላል። ድርጅቱ ለህዝብ ያለዉ ንቀት ልክ የለዉም። አንድ ወቅት አቶ አባይ የኦሮሞ ህዝብ የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ሲቃወም “ልክ እናስገባቸዋለን” ብሎ ነበር። ከዝህ የከፋ ተምክህተኝነት የለም። ህወሀት ከፈለገ ደግሞ አባባሉ "የትህትና ገላጭ " ይሆናል። እዉነቱ ግን ትክክለኛዉ ትምክህተኛ ህወሀት መሆኑ ነዉ። ጠባብነት እና ትምክህተኝነት የአንድ ህወሀት ሁለት ገፅታዎች ናቸዉ ማለት ነዉ።

አሁን ህወሀት ለስብሰባ መቀሌ ላይ ከትሟል። እነደተለመደዉ ጠባብነት እና ትምክህተኝነት ላይ መዝመቱ አይቀርም። እነዝህን ጠንቀኛ አስተሳሰቦችን በቁርጠኝነት ለመታገል ከፈለገ ደግሞ ጦርነቱን ራሱ ላይ ማወጅ አለበት። በዝህ ወቅት ዘመቻዉን በተሳሳተ ቦታ ላይ አዉጆ ጊዜዉን እና ጉልበቱን ባያባክን ጥሩ ነዉ። ከነቃ ዘመቻዉን እዝያዉ መጨረስ ይችላል። ጠባብነት እና ትምክተኝነት ከሱ ጋር ስብሰባዉ ላይ ናቸዉ። ሌላ ቦታ ሊፈልጋቸዉ አይገባም። ከአዳራሹ ውጭ ብአዴን፣ ኦህዴድ ወይም ደህዴን ጋር ከፈለጋቸዉ አያገኛቸዉም። ራሱን ተጠያቂ ካላረገ አሁንም ወር ሳይሞላ ተመልሶ መሰብሰቡ ግድ ይሆናል። ስለዝህ እዝያዉ በስብሳባ አዳራሽ ራሱን ገምግሞ የፀረ-ትምክህተኝነት እና የፀረ-ጠባብነት ትግሉን በማጠናቀቅ ዳኒኤል እንዳለዉ ለኢትዮጵያ “መድሃኒት” ቢፈልግ ጥሩ ነዉ። ለድርጅቱም ሆነ ለሀገሪቷ የሚጠቅመዉ ይህ ይመስለኛል። ማንም ላይታለልለት ሊያታልለን መጣር አይበጀዉም። ልቦና ይስጣቸዉ እንላለን።

ነፃነት፣ እኩልነት እና አንድነት ለኢትዮጵያ ህዝብ!
አንድነት ኃይላችን ነዉ!
ነፃነት ግባችን ነዉ!
Source: ጠባብነት እና ትምክህተኝነት የአንድ ህወሀት ሁለት ገፅታዎች