ጉዞ ባህርዳር ከአሰላ ቢጀምር? Marsimoi Tafa


#1

የሰሞኑ የሚዲያ ወሬ ሁሉ የኦሮሚያ ልዑካን ቡድን በአማራ ክልል ስላደረጉት ጉብኝት ነው። በሁለቱ ክልላዊ መንግስታት መካከል በተደረገው ውይይት መሰረት አፋን ኦሮሞ በአማራ ክልል የትምህርት ካሪኩለም ውስጥ በመካተት እንደ አንድ ትምህርት እንዲሰጥ እንደሚደረግና በባህር ዳር ከተማ የኦሮሞ የባህል ማዕከል እንዲከፈት መግባባት ላይ መደረሱን ሰምተናል። ይህ የሁለቱን ህዝቦች ወዳጅነት የሚያጠናክር ስራ በመሆኑ ደስ ይላል። OPDO በአዲስ አበባ እየተገበረ ያለውን ቋንቋና ባህልን የማሳደግ ስራ ወደ ሌሎች ክልሎች ዘልቆ ሊሰራ በማቀዱ ሊበረታታ ይገባል። ይህ ደግሞ ቋንቋው የፌደራል የስራ ቋንቋ እንዲሆን አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

ባህርዳር ከተማ ላይ ህፃናት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በሚያምር የህፃናት ድምፅ “A, B, C, D…”(ኣባጫዳ) ሲሉ መስማት እንዴት ያስደስታል። በተለይ dh’ን አስተካክለው ሲጠሯት ለመስማት ጓጓሁ።

ነገር ግን የABCD ድምፅ ከባህርዳር እኩል ለአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች ብርቅ ነው። የእነ ለማ መገርሳ OPDO ከባህርዳር በፊት ለተመሳሳይ ጉዳይ አሰላን፣ አዳማን፣ ጅማን መጎብኘት ነበረበት። በተለይም የሚኒልክ አጎት የራስ ዳርጌን አሰላ ሳይጎበኝ አባይን ተሻግሮ ባህርዳር ድረስ መሄድ አልነበረበትም። OPDO።
ከጠቀስኳቸው ሶስቱ ከተሞች አሰላን በሚገባ አውቃታለሁ። ኖሬባታለሁ። አሰላ ከባህርዳር እኩል ለአፋን ኦሮሞ ባዕድ ናት ያልኩበትን ጥቂት ተጨባጭ ምክንያቶች ልጥቀስ፦

በ2006 ዓ.ም ክረምት ሃምሌ ወር ውስጥ ለ15 ቀናት በተካሄደው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ስብሰባ ወቅት አሰላ በሚገኘው የአዳማ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ ግቢ ውስጥ ተሰብስበን ነበር። በስብሰባው ላይ የተካፈልን የአሰላና የአካባቢዋ ተማሪዎች ቁጥራችን 2140 እንደነበረ አስታውሳለሁ። በመጀመሪያው ቀን ስብሰባው ሲጀመር ሁሉም ተማሪዎች በአንድ አዳራሽ ተሰብስበን ኦሬንቴሽን ከተሰጠን በኋላ ‘አፋን ኦሮሞ ጭራሽ የማትሰሙ ተማሪዎች’ ቀነኒሳ ቴክኒክ ኮሌጅ ቦታ ተዘጋጅቶላችኋል ወደዚያው እንድትሄዱ ሲባል ከግማሽ በላይ ተማሪ አዳራሹን ለቆ ወጣ። ከመድረኩ ላይ “ልብ በሉ ‘አፋን ኦሮሞ ጭራሽ የማትሰሙ’ ነው የተባለው” አሉ። ምንም የተቀየረ ነገር የለም። ቀነኒሳ ኮሌጅ የተዘጋጀው ክፍል ደግሞ ከ100 ተማሪ በላይ የሚይዝ አልነበረም። የመድረኩ መሪዎች ደርቀው ቀሩ። በፍፁም ያልገመቱት ነገር ሆነ። ነገሩ ግን እውነት ነው። ይህ ኦሮሚያ ነው! ይህ አርሲ ነው! ይህ አሰላ ነው!

ልክ ስብሰባው እንዳለቀ በሶስተኛው ቀን የአሰላ ከተማ ትምህርት ፅ/ቤት ሄጄ በከተማዋ የሚገኙ የመዋዕለ ህፃናት ትምህርት ቤቶች ዴታ(data) መሰብሰብ ጀመርኩ። በወቅቱ 33 የመዋዕለ ህፃናት ት/ቤቶች ነበሩ። 33ቱም በአማርኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ ናቸው። “ቋንቋችን በእነ ምኒሊክ፣ ሃይለ ስላሴና ደርግ ሲጨቆን ነበር” እያለ የሚሰብክ የOPDO ካቢኔ ልጁ አፋን ኦሮሞ አይችልም።

ባመቱ, 2007 ዓ.ም, አርሲ ዩኒቨርሲቲ በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር የዩኒቨርሲቲው መምህራን ልጆቻቸውን የሚያስተምሩበት የመዋዕለ ህፃናት ት/ቤት አጥተው “ኑማን-Numaan” የሚባል ት/ቤት ተደራጅተው ከፈቱ። አሁንም በከተማዋ ያለው ብቸኛው የአፋን ኦሮሞ የመዋዕለ ህፃናት ትምህርት ቤት ኑማን ብቻ ነው። ይህ ኦሮሚያ ነው! ይህ አርሲ ነው! ይህ አሰላ ነው!

አሰላ ላይ በየ አመቱ የአፋን ኦሮሞ የፈተና ወረቀት ይቀደዳል። ከላይ እንደገለፅኩት ሁሉም መዋዕለ ህፃናት የሚያስተምሩት በአማርኛ ቋንቋ ሲሆን አብዛኛው የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶችም ሁሉንም የትምህርት አይነቶች በአማርኛ የሚያስተምሩና አፋን ኦሮሞ እንደ አንድ ትምህርት ብቻ የሚሰጡ ናቸው። እነዚህ ትምህርት ቤቶች የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ሲፈተኑ አፋን ኦሮሞም ይፈትናሉ። በተለምዶ ደግሞ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአፋን ኦሮሞ ፈተና በመጨረሻው ቀን ነው የሚውለው። ተማሪው ፈተናውን ጨርሶ ሲወጣ ዩኒፎርሙንና የአፋን ኦሮሞን የጥያቄ ወረቀት ቀዳደው አስፋልት ላይ እየጎዘጎዙ ወደ እየ ቤታቸው ይሄዳሉ ። የከተማው ፖሊስ በያመቱ ለዚህ ጉዳይ ብቻ ለጥበቃ ይሰማራል። እነዚህ እድሜያቸው ከ15 አመት የማይበልጥ ታዳጊ ህፃናት በወላጆቻቸውና በመምህራን ምን አይነት ፀረ ኦሮሞ አስተሳሰብ እየተጫነባቸው እንደሆነ ገምቱ። ይህ ኦሮሚያ ነው! ይህ አርሲ ነው! ይህ አሰላ ነው!

አሰላ ላይ በየ ሰፈሩ ከሚካሄዱት የእድርና የሸማቾች ማህበራት ስብሰባ ጀምሮ እስከ ትላልቅ የህዝብ ስብሰባዎች የሚካሄዱት በአፋን ኦሮሞ አይደለም።

ከተጀመረ አምስተኛ አመቱን ሊደፍን የተቃረበው ታላቁ የOromoprotest በቆይታው በሁሉም የኦሮሚያ ክፍል ተካሂዷል ሊባል ይችላል። ከኦሮሚያም አልፎ በጎንደር ከተማ አደባባዮች “በኦሮሚያ ጎዳናዎች ላይ የሚፈስ የኦሮሞ ደም የኛም ደም ነው!” የሚል የድጋፍ ሰልፍ ሰምተናል። አይተንማል። በጎንደር የተሰማው አይነት ድምፅ በአሰላ እስካሁን አልተሰማም። ይህ ኦሮሚያ ነው! ይህ አርሲ ነው! ይህ አሰላ ነው!

መልዕክቴ፦
ለእነ ለማ OPDO~ ከባርህዳር አሰላ ይቀርባል!
ለቄሮ~ አሰላም ላይ እምቦጭ አረም አለ!
Source: https://www.facebook.com/tsegaye.ararssa/posts/846835065477502
~by MarsimoiTafa