አዲስ አበባ የአፍሪካና የኢትዮጵያ ግዛት ለመሆን የኦሮሚያ አካል መሆን እንዳለባት፤ (By Betru Dibaba)

addis-ababa
constitution
oromia-special-int

#1

አዲስ አበባ የአፍሪካና የኢትዮጵያ ግዛት ለመሆን የኦሮሚያ አካል መሆን እንዳለባት፤ (By Betru Dibaba)

ብዙዎች አዲስ አበባን “ባለቤት አልባ ከተማ” ሲሉዋት እንሰማለን። ይህ ጽሁፍ አዲስ አበባ ከህገ-መንግስቱ አንጻር ያለችበትን ሁኔታ ለማስረዳት ተጻፈ።

የኢፌዲሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 2፣ ስለ የኢትዮጽያ የግዛት ወሰን “የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን የፌደራሉን አባሎች ወሰን የሚያጠቃልል ሆኖ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሰረት የተወሰ ነዉ” በማለት ይደነግጋል። ከዚሁ ድንጋጌ የምንረዳዉ በኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት ዉስጥ የፌደራል አካል ወይም ግዛት የሚባል የለም። አያይዘን መረዳት ያለብን የፌደራሉን አባላት ዝርዝር ነዉ። አንቀጽ 47 (1)፣ የፌደራል መንግስት አባላትን እንዲህ ይዘረዝራል፤

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባላት የሚከተሉት ናቸዉ፤

፩. የትግራይ ክልል፣
፪. የአፋር ክልል፣
፫. የአማራ ክልል፣
፬. የኦሮሚያ ክልል፣
፭. የሱማሌ ክልል፣
፮. የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል፣
፯. የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣
፰. የጋምቤላ ሕዝቦች ክልል፣
፱. የሐረሪ ሕዝብ ክልል።

ስለዚህ፣ የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን የዘጠኙ ክልሎች የግዛት ድምር ብቻ ነዉ። ማለትም፣ ከዘጠኙ ክልሎች ግዛት በላይ ወይም ከዘጠኙ ክልሎች ግዛት ያነሰ ኢትዮጵያ ግዛት የላትም።

ሽሬ፣ መቐለ፣ አዱዋ በክልልነት እስካልተጠቀሱ በትግራይ ክልል ስር ካልታቀፉ፣ የኢትዮጵያ ግዛት አይሆኑም። ደብረብርሃን፣ ባህርዳር፣ ደብረማርቆስ በክልልነት እስካልተጠቀሱ የአማራ ክልል አካል ካልሆኑ፣ የኢትዮጵያ አካል አይሆኑም። ድሬዳዋ፣ ነቀምቴ፣ ሱሉልታ በኦሮሚያ ካልታቀፉ፣ በኢትዮጵያ ግዛት ወሰን ሊታቀፉ አይችሉም።

አዲስ አበባ የራሷ መስተዳድር ያላት ከተማ መሆኗ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 49(2) ሰፍሯል። ይህ የነዋሪዎች እራስን በራስ ማስተዳደር መብት በከተማዋ ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/2003 አንቀጽ 7 ስር ተዘርዝሯል።
አንቀጽ 8 እና 39፣ የብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ ስያሜ፣ እውቅና፣ ብሔረሰብና ህዝብ ከተሰጣቸው መብቶች ጥቂቶቹ ናቸው፤ አንቀጽ 39(1) እና 40(3)። ነዎሪች ግን የተጠቀሱትን መብቶች ሳይሆን ራሱን በራሱ የማስተዳደር (የራሱን ዕድል እንዲወስን አይደለም) መብት ተሰጥተዋቸዋል፤ አንቀጽ 49(2)። በቻርተሩ አንቀጽ 7፣ ይህ የነዎሪዎች ራስን የማስተዳደር መብት ፡-

፩. ስለከተማው የሚወሰኑ ጉዳዮችን በሚመላከት መረጃ የማግኘት፣ ሃሳብና ጥያቄ የማቅረብ እና መልስ የማግኘት መብት አላቸው።

፪. የከተማው አስተዳደር የሚሰጠውን አገልግሎት በእኩልነት፣ በግልጽነትና በፍትሐዊነት መርህ መሰረት የማግኘት መብት አላቸው።

፫. ፖሊሲ፣ በጀት፣ የሥራ ዕቅድና መመሪያ ለነዋሪዎች ይፋ መሆን አለበት። በመሆኑም፣ የአዲስ አበባ ባለቤትነት የኦሮሚያ መሆኑን መቀበል ከክልሉ ጥቅም አንፃር ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባ ነዎሪዎችን ለብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ ወግና መብቶች ማድረስ ነው።

ከዚህም በላይ፣ አዲስ አበባ የፌደራል መንግስት ርዕሰ ከተማ፣ አንቀጽ 49(1) እና የብዙ ዓላም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫና መዳረሻ ናት። ይሁን እንጂ አዲስ አበባ በክልልነት ወይም በፌደራሉ አባልነት አልተጠቀሰችም።

የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን ከክልሎች ወይም ከፌደራል አባላት ወሰን ግዛት አንጻር ብቻ የተወሰነ መሆኑን ተመልክተናል። እንዲሁም፣ አዲስ አበባ ከተማ እንጂ ክልል እንዳልሆነች ከህገ መንግስቱ አይተናል። በዓለም ላይ፣ ‘ሀ’ የ’ለ’ ክልል አካል ነዉ፣ የሚል ህገ መንግስት የለም፤ አስፈላጊም አይደለም። ከዚህ አንጻር፣ የፌደራል ህገ መንግስታችን፣ ዓለም ላይ ካሉት ህገ መንግስታት ያለፈ ተግቷዋል። አዲስ አበባ በክልል መታቀፏን ግልጽ አድርጓል። አንቀጽ 49(5) ‘… አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ …’ የሚል ሀረግ የጠቋሚነት ሚና አለዉ። በመሆኑም፣ አንቀጽ 2 እና 47(1)ን ብቻ አንብበዉ፣ አዲስ አበባ የኦሮሚያ አካል መሆኗን ለማይረዱ፣ ሀረጉ አጋዥ ነዉ።

የማጠቃለያ ነጥቦች፦

  1. የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን የክልሎች የግዛት ወሰን ድምር ነዉ፤ አንቀጽ 2።
  2. በኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት ዉስጠ የፌደራል አካል የሚባል የለም፤ አንቀጽ 2፣ 46፣ 47።
  3. ክልሎች ዘጠኝ ብቻ ናቸዉ፤ አንቀጽ 47(1)።
  4. አዲስ አባባ ከተማ እንጂ ክልል አይደለችም፤ አንቀጽ 49(2)።
  5. አዲስ አበባ የኦሮሚያ ግዛት ናት፤ አንቀጽ 47(1፣ 4))፣ 49(5)።
  6. የአዲስ አበባ ባለቤትነት የኦሮሚያ መሆኑ የአዲስ አበባ ነዎሪዎችን ለህዝቦች ወግና መብቶች ማብቃት ነው።
  7. አዲስ አበባ የኦሮሚያ ግዛት በመሆኗ፣ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ግዛት ሙሉ ይሆናል።

~via DanielDhaba.